የፊሊጶስ አደፍርስ አጭር የሕይወት ታሪክ

ልጃችን ፊሊጶስ አደፍርስ ከአባቱ ከአቶ ፈቃደ አደፍርስ እና ከእናቱ ከወ/ሮ ሜላት ገረመው እ.ኤ.አ. ሐምሌ 22/2007 ዓ.ም በዕለተ ሰንበት ከጠዋቱ 4፡30 በሲውዲን ሀገር በስቶክሆልም ከተማ በሰደር ሹክሁስ (Södersjukhus) ሆስፖታል ተወለደ፡፡

ፊሊጶስ አንድ አመት ከስድስት ወር ሲሞላው በቀድሞ የመኖሪያ አካባቢው ስኩጎስ (Skogås) ወደሚገኘው መዋዕለ ሕጻናት መሔድ ጀምረ በዚሁም መዋዕለ ሕጻናት ስደስት አመት እስኪሞላው ድረስ ቆይቷል፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስም በአካባቢው የኤድቦ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት (Edboskola) እስከ ሶስተኛ ክፍል ድረስ ተምሯል በመቀጠለም ከአራተኛ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ድረስ ኤልቭሸ (Älvsjö) በሚገኘው አለማቀፍ እንግሊዘኛ ት/ቤት ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቷል፡፡ 

ልጃችን ፊልጶስ ገና ከልጅነት እድሜው ጀምሮ በጀምናስቲክ፣እግርኳስ፣ኢነባንዲ እንዲሁም እስኩጎስ (Skogås) በሚገኝው የማሪያ ሺርካ (Mariakyrka) የሕጻናት ዝማሪ ውስጥ ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን በተለየ መልኩ ግን ለእግር ኳስ ከፍተኛ ፍቅር የነበረው ታዳጊ ልጅ ነበር፡፡ 

ፊሊጶስ በዚሁ በስቶክሆልም ከተማ ከስድስት አመቱ ጀምሮ እስከ አስራ ሁለት አመቱ (ከ2013-2019) ዓ.ም. ድረስ በስኩጎስ ትሮንግሱንድ (Skogås-Trångsunds FF) የእግር ኳስ ቡድን ሲጫወት ቆይቶ በ2020 ዓ.ም ወደ ኤልቭሸህ አይኮ (Älvsjö AIK FF) የእግርኳስ ቡድን በመቀየር ሕይወቱ እስካለፈችበት ቀን ድረስ በአጥቂ፣በተከላካይነት እንዲሁም በበረኝነት ሲጫወት ቆይቷል፡፡ ፊሊጶስ በሲውዲን የአይኮ (AIK) ደጋፊ አንዲሁም ከእንግሊዝ የእግርኳስ ቡድኖች የአርሴናል (Aresenal) ደጋፊ እናም የሮናልዶ (Ronaldo) አድናቂ ነበር፡፡ ይህ ታዳጊ ልጃቻን ከእግርኳስ ጨዋታውም በተጨማሪ በእድሜ ክልል የተፈቀደለት የእግርኳስ ዳኛም ነበር ፡፡ ፊሊጶስ ከ2020 ዓ.ም ጀምሮ አጫጭር የዳኝነት ኮርሶችን በመወሰድ በትርፍ ሰአቱ ብዙ የእግርኳስ ጨዋታዎች ላይ በዳኝነት ሰርቷል፡፡

በተጨማሪም ፊልጶስ የእናቱና የአባቱን ቋንቋ አማርኛ ለ6 አመታት ያህል ዘወትር እሁድ ከአብሮ አደግ ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ጋር ፊደልን በመቁጠር፣የተለያዩ የአማርኛ መጽሐፍትን በማንበብ፣ ስለ ኢትዮጵያ ባሕልና ታሪክ በመማር አሳልፏል፡፡ በመሆኑም የአማርኛ ቋንቋን አቀላጥፎ የሚያወራ እንዲሁም መጻፍና ማንበብ በደንብ አድርጎ የሚችል በጣም ጎብዝ ልጅ ነበር፡፡

ፊሊጶስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሀይማኖቱን የሚወድና የሚያከበር የተባረከ ልጅ ነበር፡፡ በመሆኑም ስቶክሆልም በሚገኘው በደብረሰላም መድሀኒአለም ቤ/ክርስቲያን በ40 ቀኑ ክርስትና ከተነሳበት ዕለት ጀምሮ ቤተክርስቲያን በወላጆቹ አማካኝነት በመመላለስ፣ ስጋ ወደሙ በመቀበል፣ የሰንበት ት/ቤት በመከታተል፣ በንግስና በባዕላት ግዜያት ላይ የዝማሬ አገልግሎትን በመስጠት እንዲሁም በቅርብ ጊዜ ዘወትር አርብ በተጀመረው የታዳጊ ልጆች የሐይማኖት ትምህርት ላይ በመሳተፍ ቆይቷል፡፡ 

ልጃችን ፊሊጶስ በቤተሰቡ፣በዘመዶቹና በጓደኞቹ ዘንድ እጅግ በጣም ተወዳጅ፣ትሁት፣ሩህሩህ፣ሰውን አክባሪ፣ታዛዥ፣አርቆ አሳቢ፣ ፈጣን፣መሸነፍን የማይወድ፣ ጥሩ ልብ ያለው፣የመሪነት ባሕሪን የተላበሰ፣ፍቅር ሰጪ፣ ቀልደኛ እንዲሁም በቤተሰብ መሰባሰብ ላይ ዋና አስተባባሪ፣ ጨዋታና ደስታ የመፍጠር ልዩ ተሰጦ ሲኖረው ለሰዎች ስሜት በመጠንቀቅ ነገሮችን አስተውሎ በግልጽ በማስረዳት ብሎም ከማንኛው ሰው ጋር ታላቅ የመግባባት ችሎታ የነበረው ልጅ ነበር ፡፡ ከዚህም ችሎታው የተነሳ በልጅነቱ የመጀመሪያዎ ጥቁር የሲውድን ጠቅላይ ሚኒስትር መሆንን የሚመኝ ከዛም የሕግ ትምህርትን በመማር ለሰው ልጆች ፍትህ ማስፈን የሚፈልግ ሆኖም ግን ሕይወቱ ከማለፉ ጥቂት ወራቶች በፊት የነበረውን ሀሳብ በመቀየር ወደ ፊት ዲፕሎማት ሆኖ በኢትዮጵያና በተለያዩ ሀገራት እየተዘዋወረ መስራት እንደሚፈልግ ሲነግረን ቋይቷል፡፡ በተጨማሪም ብዙ መልካም ነገሮችን ለሀገሩ ለማበርከት ከወዲሁ የሚሻና የሚመኝ ታዳጊ ልጅ ነበር፡፡ 

ፊሊጶስ በትምህርት ቤቱም ሆነ በቅርብ ቤተሰቦቹ እንደሚነገርልት የጠቅላላ እውቀቱ ከፍተኛ የሆነ፣ የፖለቲካ ፍላጎቱና እውቀቱ የዳበረ እንዲሁም ጥሩ ተናጋሪ የሆነና ከእድሜው በላይ የበሰለ ልጅ ነበረ፡፡

ፊሊጶስ በተለየ መልኩ ለኢትዮጵያ ጥልቅ ፍቅር ያለው፣የእረፍት ጊዜ በመጣ ቁጥር እረፍቱን ኢትዮጵያ ማሳለፍ የሚወድ፣ ኢትዮጵያ ላሉ ቤተሰቦቹና ዘመዶቹ እንዲሁም ለአያቶቹ እጅግ የሚያዝንና የሚጨነቅ፣ በተለየ መልኩ ከልጅነቱ ጀምሮ ላሳደገችው እና ለተንከባከበችው ለአክስቱ ለየሺ ጥልቅ ፍቅር የነበረው ሁልጊዜ እንደሚናገረው ወደፊት እራሱን ሲችል ትልቅ ድርጅት ከፍቶ የሺን የድርጅቱ አስተዳዳሪ ማድረግ ሕልሙ ነበር፡፡ 

ልጃችን ፊሊጶስ በትምህርት ቤቱ በተማሪዎችና በመምህራን ዘንድ ታዋቂ፣በትምህርቱ ጎበዝ ፣ጓደኞቹን የሚወድ፣ጓደኞቹን የማያስነካ እንዲሁም አሳልፎ የማይሰጥ፣ በራሱ የሚተማመን ለመብቱ የቆመ ፣በጣም ተጫዋችና ቀልድ አዋቂ፣ ተጽእኖ ፈጣሪ፣ ለሀገሩና ለአለም የተለየ ነገርን ለመፍጠር ጽኑ ፍላጎት የነበረው ልጅ ነበር፡፡ 

ፊሊጶስ አደፍርስ ሁለት እህቶችና አንድ ወንድም ያለው ሲሆን በተለየም ከታናሽ እህቱ አቢጋኤል ጋር በትልቅ ፍቅር በአንድ ላይ ያደገ፣በኩራት የምታየው ትልቅ ወንድሟ፣የልብ ጓደኛዋ፣ሚስጥረኛዋ፣አርአያዋ፣በሕይወቷ ለአንድ ሳምንት እንኳን ተለይታ የማታውቀው የምትሳሳለትና እንደነብሷ የምትወደው ወንድሟ ነበር፡፡

ፈሊጶስ ለእኛ ለአባትና ለእናቱ የበኩር ልጃችን፣ እንደአይናችን ብሌን የምናየው የቤታችን ምሶሶ፣ የደስታችን ምንጭ፣ ለትልቅ ቦታ የምንጠብቀው አብረን በኖርንበት 15 ዓመታት ውስጥ ትልቅ ፍቅርን ያስተማረን ልጃችን ነው፡፡ 

በመጨረሻም በዛሬው ዕለት በዚህ ቦታ ለተገኛችሁ ቤተሰቦቻችን፣ ወዳጆቻችን አብሮ አደግ ጓደኞቹ፣መምህራኖቹ እንዲሁም በመላው ዓለም ይህን የቀብር ሥነ-ስርዓት ለምትከታተሉ በሙሉ ልናሳስብ የምንወደው ማንኛው ልጅ በዚህ ለጋ እድሜው በእንዲህ አይነት ሁኔታ ሕይወቱን ማጣት እንደሌለበት እያመንን….. ለዚህም በቀጣይ እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ በፊልጶስ አደፍርስ ስም ልናቋቋመው ባሰብነው መታሰቢያ ድርጅት ወይም ፋውንዴሽ የሁላችሁንም ሐሳብና ድጋፍ ከወዲሁ የምንሻ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

ፊሊጶስ በሕይወት እያለህ የምትወደውን ሰው ማሰባሰብና ፍቅር መስጠት አነሆም ዛሬ በሕይወት ሳትኖር ትልቁንም ትንሹንም በቅርብ በሩቅ ያለውንም የሚያቅህንም የማያቅህንም አሰባስበሀል፡፡……… ፊሊጶስ ሁሌም አሸናፊ ነህ!!!!

ፊሊጶስ በ9ክፍል የመዚጊያ የተማሪዎች መጽሔት ላይ እራስህ እንደጻፍከው 

ˮYou won’t forget my name ʺ  ………
ስሜን ሁሌም አትረሱትም። እኛም

ሁልጊዜ እንደማንረሳህ ቃል እንገባለን………

ለዘላለም በልባችን ውስጥ ትኖራለህ!!!!!!!

ፊሊጶስ ሁልጊዜም እንወድሀለን!!!

Vila i frid
Länge leve FillE